Tuesday, October 20, 2015

የሺዓና የአህሉሱና የዓሹራ ውሎ

የሺዓና የአህሉሱና የዓሹራ ውሎ

የዓሹራ ቀን፤ የፊዓአውንን ትእቢትና አምባገነነንነት ያከተመበትና ለሌሎችም መቀጣጫ የሆነበት፣ ነብዩላህ ሙሳም የተደሰቱበት ለአህሉሱና ታላቅ ትርጉም ያለው የድል ብስራት ቀን ነው። አህሉሱና ይህንን ቀን በአል አያደርጉትም። የተለየ ድግስም ሆነ አለባበስ የላቸውም። ሆኖም መልእክተኛው ﷺ በደነገጉት መሰረት ይፆሙታል፣ መልካም ተግባራትን ይፈፅሙበታል፣ ከአላህ ልዩ ምንዳን በመከጀልም በዒባዳ ያሳልፉታል።

ሺዓዎች ግን ስለ ዓሹራ ቀን ሲያስቡ ሚታወሳቸው የታላቁ ሰሀቢይ የአሊይ ኢብኑ አቢ ጣሊብ ልጅ ሁሰይን የተገደሉበት ቀን መሆኑ ብቻ ነው። ሺዓዎች በዚህ ቀን ሀዘናቸውን ለመግለፅ እራሳቸውን የሚጎዱ ብዙ ነገሮችን በስፋት ይፈፅማሉ። ጭንቅላትንና ሌሎች አካሎቻቸውን በስለት መብጣትና ማድማት (ተጥቢር)፣ ፊታቸውን መደብደብ (ለጥም፣) እራስን በሰንሰለት መግረፍና ማንገላታት፣ በእንብርክክ መሄድ፣ ብዙዎችም ዘንድ ጥቁር መልበስና የለቅሶ ሙሾ ማውረድ ብሎም በራስ ላይ ኩነኔን መጥራት የተለመዱ የአሹራ ትእይንቶቻቸው ናቸው።

በእጅጉ ይገርማል፤
ለኛ ለአህሉሱና ደስታን ሲያላብሰን፣ ተስፋን አሰንቆ ድልን ሲያበስረን፤ ለወንጀላችን ማርታን ለማግኘት  ሩጫ ውስጥ ሲከተን፤

ለሺአዎች ግና፤
የሀዘን የዋይታ፣ የውድቀት የሽንፈት ማስታወሻ፣ የተስፋ ማጨለሚያ ነው!!

ሁሰይን የነብዩ ﷺ የልጅ ልጅ በኢስላማዊ እውቀት ከመጠቁ ታላላቅ ሰሀቦች አንዱ ኗቸው። በኢባዳ ብርቱ የተወዳጇ የመልእክተኛው ﷺ ልጅ የፋጢማ ረዲየላሁ አንሀ ልጅ ናቸው። ስለዚህም ማንኛውም ሙስሊም በሁሰይን መገደል ሊያዝን ይገባል። ነገር ግን የሺአዎች አይነት የሀዘን መግለጫ መፈፀም ድንበር ማለፍ ነው። ኢስላማዊ መሰረትም የለውም፤ ብሎም የጃሂሊያ ቅሪት ነው። ዲናችን ይህንን አይነት ድንቁርና በግልፅ ለመከልከሉ ግልፅ መረጃዎች አሉን፤

عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بن مسعود رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ قَالَ : قَالَ النَّبِيُّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ : (لَيْسَ مِنَّا مَنْ لَطَمَ الْخُدُودَ وَشَقَّ الْجُيُوبَ وَدَعَا بِدَعْوَى الْجَاهِلِيَّةِ) رواه البخاري ومسلم

ከአብዱላህ ኢብኑ መስኡድ በተዘገበ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል « "ሀዘንን ለመግለፅ" ጉንጩን የመታ፣ ልብሱን የተረተረ፣ እንደ ጃሂሊያ ሰዎች ሙሾ ያወረደ ከኛ አይደለም» ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል

ለሀዘን ሲል ፊቱን ወይም ደረቱን የመታ በዚሁ ውስጥ ይካተታል። ጉንጭን መመታት በሀዲሱ ላይ ተነጥሎ የተጠቀሰው በድሮ ጊዜ የተለመደ ስለነበር ብቻ ነው።
የጃሂሊያ ሰዎች ሙሾ፤ ሟችን በማሞካሸት ማስለቀስ እንዲሁም በራስ ላይ ጥፋትን እና ኩነኔን መመኘት ነበር።

ይህ የሺዓዎች የአሹራ ትእይንት አሹራ ከተደነገገበት መንፈስ የራቀና ኢስላም የማያውቀው የጃሂሊያ ርዝራዥ መሆኑ ግልፅ ነው።

☞ ይህንንም ከላይ ከጠቀስኩት መረጃ ባሻገር በተከታዮቹ ስድስት ነጥቦች ይበልጥ ግልፅ ማድረግ ይቻላል።

1) አሹራን ሺዓዎች በሚያሳልፉት መልኩ ማሳለፍም ይሁን የነሱን ተግባር መፈፀም በኢስላም የማይታወቅ ለመሆኑ ትልቁ መረጃ በታላላቅ ሰሀቦችና በምርጥ ተከታዮቻቸው ዘመን የማይታወቅ  በታሪክ ድርሳናት ሁሉ ያልተዘከረ መሆኑ ነው። ይህ ተግባር በሸሪዓችን የተደነገገና ምንዳን የሚያስገኝ ቢሆን ሰለፎች በቀደሙን ነበር።

የዚያን ጊዜ ዲን ያልነበረን ነገር አሁን ዲን ማድረግ ፈፅሞ አይቻልም!!

2) በኢስላም ውስጥ ብዙ ታላላቅ ሰዎች አልፈዋል። መልእክተኛው ﷺ በህይወት እያሉም ተወዳጇን ባለቤታቸውን ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድን አጥተዋል። እንደ ሀምዛ ቢን አብድልሙጠሊብ፣ ጃእፈር ኢብኑ አቢ ጣሊብ፣ አብዱላህ ኢብኑ ረዋሀህ እና ሌሎችም ብዙ የሚወዷቸው ታላላቅ ሰዎችም ተሰውተዋል። ነገር ግን ለአንዳቸውም ይህ አይነቱ የሀዘን ቀን አልደነገጉም። ታዲያ በእሳቸው ዲን ከተሟላ በኃላ ድንጋጌ ይመጣልን??

3) ሁለም ሺዓዎች የሁሰይን አባት ዓሊይ ከሁሰይን እንደሚበልጡ አይጠራጠሩም። ይህ ታላቅ ሰሀቢይ የኢስላም የቁርጥ ቀን ልጅ በ40ኛው የሂጅራ አመት በረመዳን ወር ሀያ ሰባተኛዋ ቀን በጁምአ ዕለት ለሰላተል ፈጅር ሲወጣ በግፍ ተገድሏል። ሺዓዎች ሆይ! እራሳችሁን የዓሊይ ጭፍሮች (ሺዓቱ አሊይ) ነን ትላላችሁ፤ ታዲያ ሁሰይን የተገደሉበትን ቀን የሀዘን ቀን ካደረጋችሁ አሊይ ኢብኑ አቢጣሊብስ የተገደሉበትስ?
ከዓሊይ ሁሰይንን አስበለጣችሁን??

4) ከዓሊይ በፊት ታላቁ ሰሀቢይ ኡስማን እና ኡመር በአሰቃቂ ግድያ ህይወታቸው አልፏል። ከሰሀቦች ሁሉ በላጭ የሆነውና ከነብዩ በኋላ በኸሊፋነት የመሩት አቡበከርም አልፈዋል። ነገር ግን ሰሀቦች ዘንድ ለማናቸውም ይህ አይነቱ የሀዘን ቀን አልተወሰነም።
ይሁንና ከሁሉ የከፋው አለማስተዋል፤ የነብዩን ﷺ ሞት መዘንጋታቸው ነው።  ይህ የሀዘን ስርአት ህጋዊ ነው ያለ ማንኛውም ሙስሊም ከነብዩ ﷺ ሞት የበለጠ ሊያሳዝነው የሚገባ ሀዘን የለም። በእውነትም ከእሳቸው ሞት የበለጠ አደጋ ይህንን ኡማ አልገጠመውም። የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፤
((إذا أصيب أحدكم بمصيبة فليذكر مصيبته بي فإنها أعظم المصائب)) رواه الطبراني والبيهقي والبغوي وصححه الألباني بمجموع طرقه في ((السلسلة الصحيحة)) (1106).
«ከናንተ አንዳችሁ ከባድ ሙሲባ ቢገጥመው በእኔ (መሞት) ምክኒያት የሚከሰተውን ሙሲባ ያስብ። ከሙሲባዎች ሁሉ ከባዱ እሱ ነው።» ጠበራኒይ አልበገዊና አልበይሀቂይ ዘግበዉታል። በተለያዩ የሚደጋገፉ የዘገባ ሰንሰለቶች የተዘገበውን ይህንን ሀዲስ ሸይኽ አልባኒ በ "ሲልሲለቱል አሀዲስ አሰሂሀህ 1106" ሰሂህ ብለውታል።

የታላላቆችን መሞት ወይም መገደል የሀዘን ቀን መሆን አለበት ካላችሁ፤

 ከነብዩ ﷺ ሁሰይንን አስበለጣችሁን??

5) የተፈፀመባቸውን ሰቆቃና በደል የምናነሳበት ገለፃ ክርስቲያኖች ነብዩላህ ኢሳ ላይ የደረሱ በደሎችን የሚገልፁበት አይነት መሆን የለበትም። የነሱ አካሄድ ማጋነን፣ ድንበር ማለፍና ደረሰ በሚሉት በደል ምክኒያት የአላህን ስልጣን ለኢሳ መስጠት ነው። የሺአም ግድፈት ለዚህ የቀረበ ነው። የሁሰይንን ሞት ብቻ ለይቶ ለሰው ልጆች የተፈፀመ መስእዋት እንደሆነ መደስኮርና ለሀጥያት ስርየት ብቸኛ ምክኒያት አድርጎ ማሰብ የሙስሊሞች እምነት ነውን?


6) ሙሰል'ሙሰዊ «አሺአህ ወተስሂህ» (ሺዓና ተሀድሶ) በሚለው መፅሀፋቸው፤ እራስን ማድማትና በሰይፍ መሰንጠቅ ወደ ኢራንና ኢራቅ ሺዓዎች ከህንድ የመጣባቸው የአምልኮ ስርአት ሲሆን የእንግሊዝ መንግስት ህንድና አካባቢውን በቀኝ ግዛት በያዘበት ወቅት ይህንን የአምልኮ ስርዓት ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረትና ድጋፍ ያደርግ እንደነበር አትተዋል። እንዲህ አይነቱ ተግባር የኢስላምን ውብ ገፅታ ስለሚያጠለሽ የኢስላም ጠላቶች በጣም እንደሚፈልጉት ግልፅ ነው። እስከመቼ ጠላት ምኞቱን በናንተ በኩል ያሳካል??

☞ ሺዓዎች ለነዚህ መጠይቆች ግልፅ ምላሽ የላቸውም። እንደውም የሚገርመው ዓሹራን በነሱ መንገድ በሀዘን ያላሳለፈን ሁሉ፤ በሁሰይን ሞት አላዘነምና የአህሉልበይት ጠላት (ናሲቢይ) ነው በማለት ይፈርጃሉ።

ዲናችን መረጃን እንጂ ለስሜታዊነት ቦታ አይሰጥም። አልሀምዱሊላህ!  ከማልቀስና ከማስለቀስ ባለፈ ታሪክን መርምሮ የዲንን መሰረቶችም ተገንዝቦ በብርሀን መንገድ ላይ መጓዝ መታደል ነው። በኢስላማዊ መርሆዎች በመወሰን ከእንዲህ አይነቱ የጃሂሊያ ተግባር መራቅ ፈፅሞ አህሉልበይትን መጥላት አይሆንም።  አህሉሱና በሁሰይን እና በሌሎች የነብዩ ﷺ ቤተሰቦች ላይ የደረሱ በደሎች ሁሉ ያወግዛሉ። መልእክተኛውም ቀደም ብለው ሁሰይንን መከራ እንደሚያገኘው ተንብየውለት ነበር። ነገር ግን በሌሎች የነብዩ ባልደረቦችም ላይ የከፉ በደሎች መድረሳቸው መዘንጋት የለበትም። ስለሁሉም እናዝናለን። ነገር ግን ሀዘን በዲናችን እራሱን የቻለ አካሄድ አለውና ከዛ አንወጣም።

ሺዓዎች ለሁሰይንም ይሁን ለሌሎች አህለልይት የአላህን ስልጣን መስጠታቸውንና ከርሱም ውጭ የድረሱለን ጥሪ በማሰማት ለቀብር በመስገድና ጠዋፍ በማድረግ ሽርክ መፈፀማቸውን በእጅጉ የሚወገዝ የሽርክ ተግባር ነው።

ውድ አንባቢ!
የሺአዎች እካሄድ ምን ያክል አመክኒዮ የጎደለውና ጭፍን
ውዴታን ወይም ጭፍን ጥላቻን ብቻ መሰረት ያደረገ መሆኑን ልብ በል!!

አላህ ከጥመት ይጠብቀን
አቡጁነይድ ሙሀረም 12/1436 ዓ.ሂ

Tuesday, September 1, 2015

አህባሾችና አላህን ከ‘ጂሀ’ እና ከ“መካን” የማጥራት እሳቤ

አህባሾችና አላህን ከ‘ጂሀ’ እና ከ“መካን” የማጥራት እሳቤ

ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው። የአላህ ሰላምና እዝነት በመልእከተኛው ላይ የሁን። በመቀጠል፤

አላህ እንዲህ ብሏል፤
{الرَّحْمَٰنُ عَلَى الْعَرْشِ اسْتَوَىٰ} [طه : 5]
«አል ረህማን ከዓርሽ በላይ ከፍ አለ» ጣሀ 5

ለማንኛውንም ጤናማ ሙስሊም ይህንን አንቀፅ በመጥቀስ ለመሆኑ ይህንን አንቀፅ ስትሰማ፤ ‘ሰማያት አላህን ተሸክመዋል፣ ፍጥረራቱ ያካብቡታል’፣ ‘አላህ ከዓርሽ ፈላጊ ነው’ ወይም ‘አላህ በፍጥረታቱ ውስጥ ሰርጿል’ የሚሉ መጥፎ መልዕክቶችን ተረድተሀልን? ብለህ ብንጠይቀው፤ “ፈጽሞ አዕምሮዬ አላሰበዉም” እንደሚለን ግልጽ ነው።
 በፍልስፍና ልቡ ያልታወረ ማንኛውም ሙስሊም ይህንን እና መሰል መልእክቶችን ከጥመት በራቀ መልኩ እንደሚረዳው ግልጽ ነው።  በርግጥም ከዚህ ግልጽ ቁርአናዊ መልእክት ጥመትን የሚረዳ ልቡ ውስጥ በሽታ ያለበት ብቻ ነው። ስለዚህም አህሉሱና ግን አላህ ከእርሱ ክብርና ግርማ ሞገስ ጋር በሚሄድ መልኩ ከሰማያትና ከዓርሽም በላይ መሆኑን እና ከፍጥረታቱ የተለየ “ባኢን’ መሆኑን ያምናሉ።

በዚህ መልኩ ንፁህ ምልከታ ኖሮህ አላህ የተናገረውን አፅድቀህ ስትመሰክር፤ አህባሾችና ጥመትን ያወረሷቸው ቀደምት አንጃዎች «አላህ ከአርሽ በላይ ነው» ስትል በአላህ ክደሀል ይሉሀል። ለምን ብትላቸው ለአላህ ቦታ እና አቅጣጫን ስለሰጠህ ካፊር ይሉሀል። ስለዚህም ዘወትር "አላሁ መውጁዱን ቢላ መካን" የሚል ባዶ መፈክር ሀዲስ በማስመሰል ይደሰኩራሉ።

አህባሾች... የዚህን አንቀፅ ቀጥተኛ መልእክት በሰው አእምሮ የማይመጣን የጉድለት ባህሪ የሚያስገነዝብ የኩፍር መልእክት አድርገው ለምን ይረዱታል?  ሰሀቦችና ራቢዒዮች ከአላህ የመጣውን መልእክት ተቀብለው ሳይፈላሰፉ እንዳፀዱቀት አፅድቀው በማመን ፈንታ መካን እና ጂሀ የሚል ፀጉር ስንጠቃስ ለምን አስፈለጋቸው?
የነሱን መነሻና ትክክለኛውን የአህሉሱና አቋም ማወቅ ጠቃሚ ነውና ልብ ብለህ ተከታተለኝ።

በመሰረቱ "ጂሀ" እና "መካን" እነዚህ ቃላት ሸሪዓዊ መሰረት የላቸውም። ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ በቁርዓንም ይሁን በሀዲስ አናገኛቸዉም። በተመሳሳይ መልኩ ‘ሀድ’ እና ‘ጂስም’ የመሳሰሉ ጥቅል "ሙጅመል" ቃላት ሸሪዓዊ መሰረት የላቸውም። አህሉሱና በዚህም ይሁን በሌሎች ርዕሶች ላይ መረጃን መሰረት ያደረገ አካሄድ ስላላቸው እንዲህ አይነቶቹን ጥቅል ቃላት “አል አልፋዝ አል ሙጅመላህ” መነሻ አድርገው አይናገሩም መፈተኛ አያደርጓቸውም። ነገር ግን ከቢድዓ አራማጆች በኩል ሲመጡ ለማጽደቅም ይሁን ውድቅ ለማድረግ ሳይሽቀዳደሙ ቃሉን ባለበት በመተው የሚፈለግበት መልዕክት ምን እንደሆነ ይጠይቃሉ። ከምላሹም በመነሳት መልዕክቱ ሀቅ ከሆነ ያጸድቁታል፤ ሀቅ ካልሆነም ውድቅ ያደርጉታል።

ለምሳሌ፤ አንድ አህባሽ «ለአላህ ጂሀ ‘አቅጣጫ’ አታድርጉለት ይህ ኩፍር ነው» ቢልህ፤ ከዚህ ርዕስ ጋር በተያያዘ ‘ጂሀ’ የሚለውን ቃል በቁርአን እና በሀዲስ እንደማታውቀው በመንገር በዚህ ቃል ምን እንደተፈለገበት ጠይቀው። ሀሳቡ አላህ ከፍጡራኑ ሁሉ በላይ መሆኑን ማስተባበል ከሆነ ከቁርአንና ከሱና አረንዲሁም ከተፈጥሯዊ እምነት ጋር የሚጋጭ ተራ ወሬ መሆኑን ትነግረዋለህ። ነገር ግን የፍጥረተ ዓለሙ አካል የሆኑትን ስድስት አቅጣጫዎች ለአላህ መገለጫ ማድረግ የለብንም ለማለት ከሆነ ይህ የታወቀ እንደሆነ እና ይህ አይነት ትርጓሜ ያለዉን ‘ጂሀ’ ለአላህ እንደማናጸድቅ፤ ቀደወሞውንም ስለአላህ ስናወራ ዙሪያችን ያሉ አቅጣጫዎች ፍፁም እንደማይታሰቡን ታስረዳዋለህ።

{أَأَمِنتُم مَّن فِي السَّمَاء} [الملك : 16]

«ከሰማይ በላይ ያለውን ‘አላህ’ ትተማመናላችሁን?» አልሙልክ 16

ልብ በል ወንድሜ፤ ይህንን እና መሰል አንቀፆችን ሲሰሙ የቁርአንን መልእክት በቀጥታ በመጠምዘዝ ‘አላህ ከሰማይ በላይ’ መሆኑን ሲያስተባብሉ ታይና ተገርመህ ይህ ሁሉ ልፋት እና መወራጨት ምን አመጣው ብለህ ችግራቸውን ስታጠና፤ አሁንም ለአላህ ቦታ “መካን” መስጠት አይገባም የሚሉት የፍጡራን መኖሪያ የሆኑትን ሰባቱን የቅርብ ሰማያት በማሰብ እንደሆነ እንደዚሁ ‘አላህ ከፍጡራን በላይ ነው’ ሲባሉ በዙርያቸው የሚያውቋቸውን ስድስት አቅጣጫዎች በማሰብ አላህ ከጂሀ “አቅጣጫ” የጸዳ ነዉና ከፍጡራን በላይ ነው አይባልም እንደሚሉ ትረዳለህ። የስህተታቸው ሁሉ መሰረት ይህ ነው።

☞ ጀህሚያ፣ ሙዕተዚላ እንዲሁም አሻዒራ የአላህን የበላይ መሆን የሚያስተባብሉባቸው ፍልስፍናዊ መረጃዎች ሁሉ የሚያጠነጥኑት በዚህ ብዥታ ላይ ነው። መካን(ቦታ) እና ጂሀ(አቅጣጫ) ለአላህ አይገቡም በማለት የአላህን ከፍጡራኑ የበላይ መሆን ያስተባብላሉ። እውነታው ግን፤ እነሱ ለዚህ ስለ አላህ ባህሪያት ለማወቅ መነሻ ያደረጉት ከፍጥረተዓለሙ ጋር የተያያዙትን «ዉጁዲይ» ቦታ እና አቅጣጫን ነው። ስለ አላህ የሚነገሩ እውነታዎችን ሁሉ ፍጡራን ላይ በሚያያቸው ግንዛቤዎች ከሚተረጉም እውር አስተሳሰብ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

☞ አህሉሱና አላህ ከፍጡራን ሁሉ በላይ መሆኑን ያምናሉ፤ ‘ከሰማይ በላይ ነው’ ወይም ‘ከዓርሽ በላይ ነው’ የሚለዉን ሁሉ አላህ በነገራቸው መሰረት ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ ይቀበሉታል። ስላልተነገራቸው የባህሪ ምንነት ‘ከይፊያ’ ግን ምንም አይናገሩም።  አህሉሱና ከአላህ ባህሪያት ጋር በተያዘ ፍጡራዊ የሆኑትን ጂሀ እና መካን ለአላህ አያጸድቁም።
ቁርአናዊውን የ‘ዑሉው’ አስተምህሮ ተቀብለው ሲያፀድቁም፤ ሙዓጢላዎች እንደሚያስቡት...

✘ አላህ አንደኛ ሁለተኛ ተብሎ በሚቆጠረው የመላዕክት መኖሪያ ሰማይ ላይ ይኖራል እያሉ አይደለም። መላዕክትም በሰማይ ሰዎች በመሬት በሚኖሩበት መልኩ አላህም በሰማይ ይኖራል የሚል እምነት ያለው ሰው በእርግጥም በአላህ ክዷል።

✘ እንደዚሁ ሰማይ አላህን ይሸከመዋል ወይም ያካብበዋል ከሚልም አስተሳሰብ የጸዱ ናቸው። ይህ የአላህን ከፍጥረታቱ ጋር መቀላቀልን “ሁሉል” የሚያምኑ የቢድዓ አራማጆች እምነት ነው።

✘ አላህ በፍጥረተዓለሙ ዉስጥ በሚገኙት ስድስት አቅጣጫዎች ይገለጻል፤ ፍጥረተአለሙም ያካብበዋል ማለትን ፈፅሞ አያመላክትም። ይህንን ያለ ሰውም በአላህ ላይ ውሸትን ተናግሯል፣ መንገድንም ስቷል።
አህሉሱና ይህ ሁሉ ጥመት ስለመሆኑ አይወዛገቡም።
የአላህ ከፍጥረታት በላይ መሆን አላህ በተፈጥሮ በልባችን ያኖረው ግልጽ እምነት ነውና። አላህ በቁርአን እንደገለፀው የአላህን ከፍጥረታት በላይ መሆን "ዑሉው" መግልጽ ብቻ ለአህሉሱና በቂ ነው።  በቁርአንም ላይ የምናገኘው አካሄድ ይኸው ነው። ‘አላህን ከጉድለትና ከመመሳሰል ማጥራት’ ጥቅል በሆነ መልኩ ሲቀርብ ፤ የአላህን ባህሪያት ማጽደቅ ግን በዝርዝር ሲቀርብ እናገኛለን። ለአብነት ያክል ተከታዩን መልእክት እናስተውል፤

لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ} الشور : 11
 ‹‹የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡» (አል ሹራ 11)   

ይህ አንቀፅ በየትኛውም ሁኔታ በፍጡራንና በፈጣሪ መካከል መመሳሰል እንደሌለና አላህ ሰሚና ተመልካች መሆኑን ያሳያል፡፡ መስሚያና መመልከቻ የብዙ ፍጡራን መገለጫዎች ቢሆኑም ነገር ግን የአላህ መስሚያና መመልከቻ ከፍጡራኑ ጋር አይመሳሰልም፡፡ በመስሚያና በመመልከቻ አምሳያ እንዳሌለው ሁሉ በሌሎችም ባህሪያቱ አምሳያ የለውም፡፡  ይህ አንቀጽ ሙስሊሞች ለአላህ የማይገቡ ባህሪያትን ከመረዳት አንጻር ሊኖራቸው ለሚገባው ትክክለኛ አካሄድ በመርህ መልክ ይቀርጻል።  አንቀጹ የጉድለት ባህሪዎችን ጥቅል በሆነ መልኩ ዉድቅ ሲያደርግ ምሉዕ ባህሪዎችን ግን በዝርዝር ያጸድቃል።

   አቅጣጫዎች ህዋሳዊ ማነጻጸሪያ reference point በመጠቀም ብቻ የሚታወቁ ናቸው። ማንኛውም ሰው የቂብላን አቅጣጫ ለማወቅ ጸሀይን ማነጻጸሪያ እንደሚያደርገው ማለት ነው። ሰዎች በአዕምሮአቸው የሚቀርጿቸው ማነጻጸሪያዎች ሁሉ በፍጥረተ አለሙ የተገደቡ በመሆናቸው ስለአላህ ለመናገር እነዚህን ፍጡራዊ ማነጻጸሪያዎችን መጠቀም አይገባም።

፨ አህሉሱና ፍልስፍዎችን በቁርአን እና በሱና ላይ አይሾሙም። አላህ ለራሱ ያጸደቃቸውን ባህሪዎች ያጸድቃሉ፤ ለአላህ ተገቢዉን ክብር ስለሚሰጡ ስለባህሪዎቹ የተነገሩ መረጃዎችን የፍጡራንን ባህሪ በሚረዱበት ሁኔታ አይረዱም። ሁልጊዜ መነሻቸው አላህን ከጉድለትና ከመመሳሰል ማጽዳት ስለሆነም እነዚህና መሰል የአስተሳሰብ ግድፈቶች አይገጥሟቸውም ።
አዎን! አላህን በጉድለትም ይሁን ከፍጡራን ጋር በመመሳሰል ከመግለፅ የፀዱ ናቸው።

በአንፃሩ አህባሾችና አርአያዎቻቸው ጀህሚዮች ግን ሁሌም መነሻቸው ስለ አላህ የተነገሩ መረጃዎችን ልክ ፍጡራን ላይ በሚያውቋቸው ባህሪያት መልኩ መረዳት ስለሆነ አላህን ከፍጡራን መለየት ያልቻሉ "ሙመሲላህ" አመሳሳዮች እነሱው ናቸው።

የሰማያትና የምድር ፈጣሪ አምላክ ሰለሆነው አላህ ሲነገር እንዴት ፍጡራዊ የሆኑ ባህሪዎች ይታወሳሉ??

አላህ ከጥመት ይጠብቀን!

አቡጁነይድ
ዙልቂእዳ 17/1436 ዓ.ሂ

Saturday, August 8, 2015

አምባር እና ሌሎች የሚጠለቁ ነገሮችን እጅ ወይም አንገት ላይ ማሰር እንዴት ይታያል?

አምባር እና ሌሎች የሚጠለቁ ነገሮችን እጅ ወይም አንገት ላይ ማሰር እንዴት ይታያል?
       በአቡጁነይድ ሳላህ አህመድ



ዓረቦች ከኢስልምና በፊት በነበረው የድንቁርና ዘመን ክፋትን ለመመከት፣ መልካምን ለማግኘት ወይም ከቡዳ ለመጠበቅ ሲሉ አንባርና የመሳሰሉትን ነገሮች ያደርጉት ነበር፡፡  አላህ እንዲህ ብሏል፡-

وَلَئِن سَأَلْتَهُم مَّنْ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ لَيَقُولُنَّ اللَّهُ قُلْ أَفَرَأَيْتُم مَّا تَدْعُونَ مِن دُونِ اللَّهِ إِنْ أَرَادَنِيَ اللَّهُ بِضُرٍّ هَلْ هُنَّ كَاشِفَاتُ ضُرِّهِ أَوْ أَرَادَنِي بِرَحْمَةٍ هَلْ هُنَّ مُمْسِكَاتُ رَحْمَتِهِ قُلْ حَسْبِيَ اللَّهُ عَلَيْهِ يَتَوَكَّلُ الْمُتَوَكِّلُونَ

«ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን (ጣዖታት) አያችሁን? (ንገሩኝ) አላህ በጉዳት ቢፈልገኝ እነርሱ ጉዳቱን ገላጮች ናቸውን? ወይስ በችሮታው ቢፈቅደኝ እነርሱ ችሮታውን አጋጆች ናቸውን?» በላቸው፡፡ «አላህ በቂዬ ነው፡፡ በእርሱ ላይ ተመኪዎች ይመካሉ» በል፡፡ (አል ዙምር 38)

በሌላም አንቀጽ እንዲህ ይላል፦
قُلِ ادْعُوا الَّذِينَ زَعَمْتُم مِّن دُونِهِ فَلَا يَمْلِكُونَ كَشْفَ الضُّرِّ عَنكُمْ وَلَا تَحْوِيلًا

«እነዚያን ከእርሱ ሌላ (አማልክት) የምትሏቸውን ጥሩ፡፡ ከእናንተም ላይ ጉዳትን ማስወገድን (ወደ ሌላም) ማዞርንም አይችሉም» በላቸው፡፡  አል ኢስራህ 56

አምባር፣ ክርና የመሳሰሉትን ማጥለቅ ሸሪዓዊ ድንጋጌው ሀራም (ክልክል) ነው። አንድ ሰው አምባር ሲያደርግ በራሱ ያለ አላህ ፈቃድ ተፅእኖ ያሳድራል የሚል እምነት ካለው ከአላህ ውጭ አስተናባሪ ጌታ አለ ማለቱ በመሆኑ በአላህ ጌትነት ላይ ትልቁን ሽርክ አጋርቷል ማለት ነው::

ከዒምራን ኢብኑ ሁሰይን እንደተዘገበው ‹‹ነብዩ አንድ ሰውዬ እጁ ላይ ከመዳብ የሆነ አምባር አጥልቆ ሲያዩት፤  “ይህ ምንድነው?” ብለው ጠየቁት “ለድካም በሽታ ነው” አላቸው:: እሳቸውም እንዲህ በማለት ወቀሱት “አውልቃት! ድካምን እንጂ አትጨምርልህም። እጅህ ላይ እያለች ከሞትክ አትድንም፡፡››  አል ኢማም አህመድ ዘግበውታል

ከሁዘይፋ ኢብኑል የማን እንደተዘገበው ‹‹አንድን ሰው በመታመሙ እጁ ላይ ክር አስሮ አየውና ከበጠሰበት በኋላ ይህን አንቀጽ አነበበ፦
وَمَا يُؤْمِنُ أَكْثَرُهُم بِاللَّهِ إِلَّا وَهُم مُّشْرِكُونَ
‹‹አብዛኞቻቸውም፤ እነሱ አጋሪዎች ኾነው እንጂ በአላህ አያምኑም፡፡›› (ዩሱፍ 1ዐ6)

☞ አንዳንዶች ለደም ዝውውር እና ጤናዊ አላማ ነው የምናደርገው ይላሉ፤ እስካሁን ድረስ ለጤና ያለውን ጥቅም በተጨባጭ በመረጃና በሙከራ ያረጋገጠ ጥናት የለም። ፈውስ ሁሉ ከአላህ ነው። አላህ ፈውስ ካላደረገው ነገር ፈውስን መፈለግ ከባድ ስህተት ነው። ኢብራሂም አለይሂሰላም ይህንን እውነታ ለአጋሪዎች ሲያስረዱ ተከታዩን ብለው ነበር።

«وَإِذَا مَرِضْتُ فَهُوَ يَشْفِين»ِ الشعراء ٨٠
«በታመምኩም ጊዜ እርሱ ያሽረኛል፡፡» ሹዓራዕ 80

 በዚህ መልኩ አንድ ሰው የነገሮች ሁሉ ተፈፃሚነት በአላህ እጅ እንደሆነና ያጠለቀው ነገር ግን ለፈውስ ምክንያት ብቻ እንደሆነ ቢያምን ደግሞ ትንሹን ሽርክ ፈፅሟል፡፡ ምክንያቱም ሰበብ ያልሆነን ነገር እንደሰበብ ቆጥሮ በልቡና በስራውም ከአላህ ሌላ ወደሆነ አካል ዞሯል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ትልቁ ሽርክ ለመሸጋገር በር የሚከፍት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ሸይኽ ኡሰይሚን እንዲህ ብለዋል፤
«وما لم يثبت كونه سببا شرعيا ولا حسيا لم يجز أن يجعل سببا ، فإن جعله سببا نوع من منازعة الله تعالى في ملكه وإشراك حيث شارك الله تعالى في وضع الأسباب لمسبباتها» مجموع الفتاوى 1/144

« ሸሪዓዊ ወይም ተጨባጭ የፈውስ ምክኒያት ያልሆነን ነገር ለፈውስ ምክኒያት አድርጎ መቁጠር አይፈቀድም። የፈውስ ምክኒያት አድርጎ መቁጠር የአላህን ስልጣን መቀናቀንና ማጋራትም ይሆናል።»

☞ አምባርን በዘመናችን በተለያየ ቅርፅና ይዘት እየተሰራ ወንዶች ለጌጥ በሚል ሰበብ እያደረጉት ይታያል። ታላቁ አሊም ሸይኽ ፈውዛን ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው፤ ከችግር ያድናል ብሎ ካደረገው ኩፍር መሆኑን ለጌጥ የሚለውም ሁለት ችግሮች እንደማያጡት ተናግረዋል። እነሱም ከካፊሮች ጋር ወይም ከሴቶች ጋር መመሳሰል ነው።

አላህ ከጥፋት ሁሉ ይጠብቀን!


www.fb.com/emnetihintebiq